Tuesday, February 16, 2010

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 1።

1፤ አክዓብም ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።

2፤ አካዝያስም በሰማርያ በሰገነቱ ላይ ሳለ ከዓይነ ርግቡ ወድቆ ታመመ፤ እርሱም። ሂዱ ከዚህም ደዌ እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ ብሎ መልእክተኞችን ላከ።

3፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን። ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን?

4፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ።

5፤ መልእክተኞችም ወደ አካዝያስ ተመለሱ፥ እርሱም። ለምን ተመለሳችሁ? አላቸው።

6፤ እነርሱም። አንድ ሰው ሊገናኘን መጣና። ሂዱ፥ ወደ ላካችሁም ንጉሥ ተመልሳችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ የላከህ በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በሉት አለን አሉት።

7፤ እርሱም። ሊገናኛችሁ የወጣው፥ ይህንስ ቃል የነገራችሁ ሰው መልኩ ምን ይመስላል? አላቸው።

8፤ እነርሱም። ሰውዮው ጠጕራም ነው፥ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት። እርሱም። ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ።

9፤ ንጉሡም የአምሳ አለቃውን ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፥ ወደ እርሱም ወጣ፤ እነሆም፥ በተራራ ራስ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ውረድ ይልሃል አለው።

10፤ ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች።

11፤ ደግሞም ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከበት፤ እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ፈጥነህ ውረድ ይላል ብሎ ተናገረ።

12፤ ኤልያስም። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። የእግዚአብሔርም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች።

13፤ ደግሞም ሦስተኛ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፤ ሦስተኛውም የአምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበረከከና። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ነፍሴና የእነዚህ የአምሳው ባሪያዎችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።

14፤ እነሆ፥ እሳት ከሰማይ ወርዳ የፊተኞቹን ሁለቱን የአምሳ አለቆችና አምሳ አምሳውን ሰዎቻቸውን በላች፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን ብሎ ለመነው።

15፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን። ከእርሱ ጋር ውረድ፥ አትፍራውም አለው። ተነሥቶም ከእርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ።

16፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ መልእክተኞችን ልከሃልና ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም አለው።

17፤ ኤልያስም እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ። ልጅም አልነበረውምና በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ልጅ በኢዮራም በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

18፤ አካዝያስ ያደረገው የቀረው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 2።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ።

2፤ ኤልያስም ኤልሳዕን። እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ አለው። ኤልሳዕም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ።

3፤ በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ አላቸው።

4፤ ኤልያስም። ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ።

5፤ ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ ብሎ መለሰ።

6፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ሁለቱም ሄዱ።

7፤ ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር።

8፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።

9፤ ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን። ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም። መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።

10፤ እርሱም። አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ።

11፤ ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።

12፤ ኤልሳዕም አይቶ። አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።

13፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ።

14፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና። የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።

15፤ ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።

16፤ እነርሱም። እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን አሉት። እርሱም። አትስደዱ አላቸው።

17፤ እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ። ስደዱ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም።

18፤ በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም። አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው።

v19፤ የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን። እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውኃው ግን ክፉ ነው፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች አሉት።

20፤ እርሱም። አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፥ ጨውም ጨምሩበት አለ፤ ያንንም አመጡለት።

21፤ ውኃው ወዳለበቱም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም አለ።

22፤ ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል።

23፤ ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት።

24፤ ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው።

25፤ ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፥ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 3።

1፤ በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፥ አሥራ ሁለትም ዓመት ነገሠ።

2፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ያሠራውን የበኣልን ሐውልት አርቆአልና እንደ አባቱና እንደ እናቱ አልነበረም።

3፤ ነገር ግን እስራኤልን ባሳታቸው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ተያዘ፤ ከእርሱም አልራቀም።

4፤ የሞዓብም ንጉሥ ሞሳ ባለ በጎች ነበረ፤ ለእስራኤልም ንጉሥ የመቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ አውራ በጎች ጠጕር ይገብርለት ነበር።

5፤ አክዓብም ከሞተ በኋላ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

6፤ በዚያም ጊዜ ንጉሡ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ እስራኤልን ሁሉ አሰለፈ።

7፤ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥ። የሞዓብ ንጉሥ ዐምፆብኛልና ከእኔ ጋር በሞዓብ ላይ ለሰልፍ ትሄዳለህን? ብሎ ላከ። እርሱም። እወጣለሁ፤ እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለ።

8፤ ደግሞም። በምን መንገድ እንሄዳለን? አለ፤ እርሱም። በኤዶምያስ ምድረ በዳ መንገድ ብሎ መለሰ።

9፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ የኤዶምያስም ንጉሥ ሄዱ፤ የሰባትም ቀን መንገድ ዞሩ፤ ለሠራዊቱና ለተከተሉአቸውም እንስሶች ውኃ አልተገኘም።

10፤ የእስራኤልም ንጉሥ። ወዮ! እግዚአብሔር በሞዓብ እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ እነዚህን ሦስቱን ነገሥታት ጠርቶአልና ወዮ አለ።

11፤ ኢዮሣፍጥም። በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ። ከእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎች አንዱ። በኤልያስ እጅ ላይ ውኃ ያፈስስ የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ ብሎ መለሰ።

12፤ ኢዮሣፍጥም። የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል አለ። የእስራኤል ንጉሥና ኢዮሣፍጥ የኤዶምያስም ንጉሥ ወደ እርሱ ወረዱ።

13፤ ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። አይደለም፥ በሞዓብ እጅ ይጥላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶአል አለው።

14፤ ኤልሳዕም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ያላፈርሁ ብሆን ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር።

15፤ አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ አለ። ባለ በገናውም በደረደረ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ መጣችበት፤

16፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፈሩ።

17፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።

18፤ ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው፤ ደግሞም ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣል።

19፤ የተመሸጉትንና ያማሩትን ከተሞች ሁሉ ትመታላችሁ፥ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ትቈርጣላችሁ፥ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ትደፍናላችሁ፥ መልካሞችንም እርሻዎች ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ።

20፤ በነጋውም የቍርባን ጊዜ ሲደርስ፥ እነሆ፥ ውኃ በኤዶምያስ መንገድ መጣ፥ ምድሪቱም ውኃ ሞላች።

21፤ ሞዓባውያንም ሁሉ ነገሥታት ሊወጉአቸው እንደ መጡ በሰሙ ጊዜ በወገባቸው ሰይፍ የሚታጠቁ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም በአገሩ ድንበር ላይ ቆሙ።

22፤ ማልደውም ተነሡ፤ ፀሐይም በውኃው ላይ አንጸባረቀ፥ ሞዓባውያንም በፊታቸው ውኃው እንደ ደም ቀልቶ አዩና። ይህ ደም ነው፤

23፤ በእርግጥ ነገሥታት እርስ በርሳቸው ተዋጉ፥ እርስ በርሳቸውም ተጋደሉ፤ ሞዓብ ሆይ፥ እንግዲህ ወደ ምርኮህ ሂድ አሉ።

24፤ ወደ እስራኤል ሰፈር በመጡ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው ሞዓባውያንን መቱ፥ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ፤ ሞዓባውያንንም እየመቱ ወደ አገሩ ውስጥ ገቡ።

25፤ ከተሞችንም አፈረሱ፤ በመልካሞቹም እርሻዎች ሁሉ ላይ እስኪሞሉ ድረስ እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ድንጋይ ይጥል ነበር፤ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ደፈኑ፥ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ቈረጡ፤ የቂርሐራሴትን ድንጋዮች ብቻ አስቀሩ፤ ባለ ወንጭፎች ግን ከብበው መቱአት።

26፤ የሞዓብም ንጉሥ ሰልፍ እንደ በረታበት ባየ ጊዜ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰባት መቶ ሰዎች ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ ወደ ኤዶምያስም ንጉሥ ያልፉ ዘንድ ሞከሩ፤ አልቻሉምም።

27፤ በዚያም ጊዜ በእርሱ ፋንታ ንጉሥ የሚሆነውን የበኵር ልጁን ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በቅጥሩ ላይ አቀረበው። በእስራኤልም ዘንድ ታላቅ ቍጣ ሆነ፤ ከዚያም ርቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ።

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 4።

1፤ ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት። ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።

2፤ ኤልሳዕም። አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም። ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች።

3፤ እርሱም። ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም አላት።

4፤ ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ አለ።

5፤ እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፥ እርስዋም ትገለብጥ ነበር።

6፤ ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን። ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፤ እርሱም። ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ።

7፤ መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም። ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ አለ።

8፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።

9፤ ለባልዋም። ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ።

10፤ ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው።

11፤ አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ዐረፈ።

12፤ ሎሌውንም ግያዝን። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው።

13፤ በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። እርሱም። እነሆ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ፤ አሁንስ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን? በላት አለው፤ እርስዋም። እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ ብላ መለሰች።

14፤ እርሱም። እንግዲህ ምን እናድርግላት? አለ። ግያዝም። ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሸምግሎአል ብሎ መለሰ።

15፤ እርሱም። ጥራት አለ። በጠራትም ጊዜ በደጃፉ ቆመች።

16፤ እርሱም። በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ አለ፤ እርስዋም። አይደለም ጌታዬ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ አለች።

17፤ ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች።

18፤ ሕፃኑም አደገ፥ አንድ ቀንም እህል አጫጆች ወዳሉበት ወደ አባቱ ወጣ።

19፤ አባቱንም። ራሴን ራሴን አለው፤ እርሱም ሎሌውን። ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው አለው።

20፤ አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበትዋም ላይ እስከ ቀትር ድረስ ተቀመጠ፥ ሞተም።

21፤ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፥ በሩንም ዘግታበት ወጣች።

22፤ ባልዋንም ጠርታ። ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እመለስ ዘንድ አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ አለችው።

23፤ እርሱም። መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጂበታለሽ? አለ። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።

24፤ አህያውንም አስጭና ሎሌዋን። ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ አለችው።

25፤ እንዲሁም ሄደች፥ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጣች። የእግዚአብሔርም ሰው ከሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፥ እነኋት ሱነማዊቲቱ መጣች፤

26፤ ትቀበላትም ዘንድ ሩጥና። በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት አለው። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።

27፤ ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም አለ።

28፤ እርስዋም። በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም አታታልለኝ አላልሁህምን? አለች።

29፤ ግያዝንም። ወገብህን ታጠቅ፥ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፥ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር አለው።

30፤ የሕፃኑም እናት። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! አልተውህም አለች፤ ተነሥቶም ተከተላት።

31፤ ግያዝም ቀደማቸው፥ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ። ሕፃኑ አልነቃም ብሎ ነገረው።

32፤ ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።

33፤ ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።

34፤ መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ።

35፤ ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።

36፤ ግያዝንም ጠርቶ። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው። ጠራትም፥ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ። ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ አላት።

37፤ ገብታም በእግሩ አጠገብ ወደቀች በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች።

38፤ ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልገላ መጣ፥ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፥ ሎሌውንም። ታላቁን ምንቸት ጣድ፥ ለነቢያት ልጆችም ወጥ ሥራ አለው።

39፤ አንዱም ቅጠላቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፥ የምድረበዳውንም ሐረግ አገኘ ከዚያም የበረሀ ቅል ሰበሰበ፥ ልብሱንም ሞልቶ ተመለሰ፥ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም።

40፤ ሰዎቹም ይበሉ ዘንድ ቀዱ፤ ወጡንም በቀመሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ ሞት አለ ብለው ጮኹ፤ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም።

41፤ እርሱም። ዱቄት አምጡልኝ አለ፤ በምንቸቱም ውስጥ ጥሎ። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ቅዱ አለ። በምንቸቱም ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም።

42፤ አንድ ሰውም ከበኣልሻሊሻ የበኵራቱን እንጀራ፥ ሀያ የገብስ እንጀራ፥ የእህልም እሸት በአቁማዳ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ፤ እርሱም። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።

43፤ ሎሌውም። ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው እሰጣለሁ? አለ። እርሱም። ይበላሉ ያተርፋሉም ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።

44፤ እንዲሁም በፊታቸው አኖረው፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል በሉ፥ አተረፉም።

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 5።

1፤ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ፤ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ፥ ነገር ግን ለምጻም ነበረ።

2፤ ከሶርያውያንም አገር አደጋ ጣዮች ወጥተው ነበር፥ ከእስራኤልም ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማርከው ነበር፤ የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር።

3፤ እመቤትዋንም። ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት።

4፤ ንዕማንም ገብቶ ለጌታው። ከእስራኤል አገር የሆነች አንዲት ብላቴና እንዲህና እንዲህ ብላለች ብሎ ነገረው።

5፤ የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን። ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ አለው። እርሱም ሄደ፥ አሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወርቅ፥ አሥርም መለውጫ ልብስ በእጁ ወሰደ።

6፤ ለእስራኤልም ንጉሥ። ይህች ደብዳቤ ወደ አንተ ስትደርስ ባሪያዬን ንዕማንን ከለምጹ ትፈውሰው ዘንድ እንደ ሰደድሁልህ እወቅ የሚል ደብዳቤ ወሰደ።

7፤ የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያትም እንደሚፈልግብኝ እዩ አለ።

8፤ የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ። ልብስህን ለምን ቀደድህ? ወደ እኔ ይምጣ፥ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ።

9፤ ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ።

10፤ ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ።

11፤ ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፥ እንዲህም አለ። እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።

12፤ የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ።

13፤ ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት።

14፤ ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ።

15፤ እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመለሰ፥ ወጥቶም በፊቱ ቆመና። እነሆ፥ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ፤ አሁንም ከባሪያህ በረከት ትቀበል ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።

16፤ እርሱም። በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ።

17፤ ንዕማንም። እኔ ባሪያህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር እንድወስድ እሺ ትለኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

18፤ እግዚአብሔርም ለእኔ ለባሪያህ በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬሞን ቤት በገባ ጊዜ፥ እኔም በሬሞን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር ለእኔ ለባሪያህ ይቅር ይበለኝ አለ።

19፤ እርሱም። በደኅና ሂድ አለው። አንድ አግድመትም ያህል ከእርሱ ራቀ።

20፤ የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ግያዝ። ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፥ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተ ኋለው እሮጣለሁ፥ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ አለ።

21፤ ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ። ሁሉ ደኅና ነውን? አለው።

22፤ እርሱም። ደኅና ነው። አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑት ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋል፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ አለ።

23፤ ንዕማንም። ሁለት መክሊት ትወስድ ዘንድ ይፈቀድልህ አለ፤ ግድ አለውም፤ ሁለቱንም መክሊት ብር በሁለት ከረጢት ውስጥ አሰረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ።

24፤ ወደ ኮረብታውም በመጣ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ፥ እነርሱም ሄዱ።

25፤ እርሱ ግን ገብቶ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም። ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም አለ።

26፤ እርሱም። ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ብሩንና ልብሱን፥ የወይራውንና የወይኑን ቦታ፥ በጎችንና በሬዎችን፥ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ትቀበል ዘንድ ይህ ጊዜው ነውን?

27፤ እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ፥ ለዘላለምም በዘርህ ላይ ይጣበቃል አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 6።

1፤ የነቢያትም ልጆች ኤልሳዕን። እነሆ፥ በፊትህ የምንቀመጥበት ስፍራ ጠብቦናል።

2፤ ወደ ዮርዳኖስም እንሂድ፥ ከእኛም እያንዳንዱ ከዚያ ምሰሶ ያምጣ፥ የምንቀመጥበትንም ስፍራ በዚያ እንሥራ አሉት፤ እርሱም። ሂዱ አለ።

3፤ ከእነርሱም አንዱ። አንተ ደግሞ ከእኛ ከባሪያዎችህ ጋር ለመሄድ ፍቀድ አለ። እርሱም። እሄዳለሁ አለ።

4፤ ከእነርሱም ጋር ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ እንጨት ቆረጡ።

5፤ ከእነርሱም አንዱ ምሰሶውን ሲቆርጥ የምሳሩ ብረት ወደ ውኃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም። ጌታዬ ሆይ፥ ወየው! ወየው! የተዋስሁት ነበረ ብሎ ጮኽ።

6፤ የእግዚአብሔርም ሰው። የወደቀው ወዴት ነው? አለ ስፍራውንም አሳየው፤ እንጨትም ቆርጦ በዚያ ጣለው፥ ብረቱም ተንሳፈፈ።

7፤ እርሱም። ውሰደው አለ፤ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው።

8፤ የሶርያም ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከባሪያዎቹም ጋር ተማክሮ። በዚህ ተደብቀን እንሰፍራለን አለ።

9፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ።

10፤ የእስራኤልም ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ነገረው ስፍራ ሰደደ፤ አንድ ጊዜም ሳይሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይሆን በዚያ ራሱን አዳነ።

11፤ የሶርያም ንጉሥ ልብ ስለዚህ እጅግ ታወከ፤ ባሪያዎቹንም ጠርቶ። ከእኛ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ አትነግሩኝምን? አላቸው።

12፤ ከባሪያዎቹም አንዱ። ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ።

13፤ እርሱም። ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችሁ ወዴት እንደ ሆነ እዩ አለ። እነርሱም። እነሆ፥ በዶታይን አለ ብለው ነገሩት።

14፤ ወደዚያም ፈረሶችንና ሰረገሎችን እጅግም ጭፍራ ሰደደ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ።

15፤ የእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ጭፍራና ፈረሶች ሰረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም። ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እናደርጋለን? አለው።

16፤ እርሱም። ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ አለው።

17፤ ኤልሳዕም። አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።

18፤ ወደ እርሱም በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ። ይህን ሕዝብ ዕውር ታደርገው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ቃል ዕውር አደረጋቸው።

19፤ ኤልሳዕም። መንገዱ በዚህ አይደለም፥ ከተማይቱም ይህች አይደለችም፤ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ አላቸው፤ ወደ ሰማርያም መራቸው።

20፤ ወደ ሰማርያም በገቡ ጊዜ ኤልሳዕ። አቤቱ፥ ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዓይኖች ግለጥ አለ፤ እግዚአብሔርም ዓይኖቻቸውን ገለጠ፥ እነርሱም አዩ። እነሆም፥ በሰማርያ መካከል ነበሩ።

21፤ የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ አልሳዕን። አባቴ ሆይ፥ ልግደላቸውን? ልግደላቸውን? አለው።

22፤ እርሱም። አትግደላቸው፤ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኸውን ትገድል ዘንድ ይገባሃልን? እንጀራና ውኃ በፊታቸው አኑርላቸው፥ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይሂዱ አለው።

23፤ ብዙም መብል አዘጋጀላቸው፤ በበሉና በጠጡ ጊዜም አሰናበታቸው፥ እነርሱም ወደ ጌታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ የሶርያ አደጋ ጣዮች ወደ እስራኤል አገር አልመጡም።

24፤ ከዚያም በኋላ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፥ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት።

25፤ በሰማርያም ታላቅ ራብ ሆኖ ነበር፤ እነሆም፥ የአህያ ራስ በአምሳ ብር፥ የርግብም ኩስ የጎሞር ስምንተኛ የሚሆን በአምስት ብር እስኪሸጥ ድረስ ከበቡአት።

26፤ የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ በተመላለሰ ጊዜ አንዲት ሴት ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እርዳኝ ብላ ወደ እርሱ ጮኸች።

27፤ እርሱም። እግዚአብሔር ያልረዳሽን እኔ እንዴት እረዳሻለሁ? ከአውድማው ወይስ ከመጥመቂያው ነውን? አለ።

28፤ ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት፤ እርስዋም። ይህች ሴት። ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ።

29፤ ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም። እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው ብላ መለሰችለት።

30፤ ንጉሡም የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥርም ይመላለስ ነበር፤ ሕዝቡም በስተ ውስጥ በሥጋው ላይ ለብሶት የነበረውን ማቅ አዩ።

31፤ ንጉሡም። የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በላዩ ያደረ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ አለ።

32፤ ኤልሳዕ ግን በቤቱ ተቀምጦ ነበር፥ ሽማግሌዎችም ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር፤ ንጉሡ ሰው ላካ፤ መልእክተኛውም ገና ሳይደርስ ለሽማግሌዎች። ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቈርጥ ዘንድ እንደ ላከ እዩ፤ መልእከተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው አላቸው።

33፤ ሲናገራቸውም መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ፤ እርሱም። እነሆ፥ ይህ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ እግዚአብሔርን ገና እጠብቅ ዘንድ ምንድር ነኝ? አለ።

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ

ምዕራፍ 7።

1፤ ኤልሳዕም። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል አለ።

2፤ ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ። ፕ

3፤ በበሩም መግቢያ አራት ለምጻም ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም። እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን?

4፤ ወደ ከተማ እንገባ ዘንድ ብንወድድ ራብ በከተማ አለ፥ በዚያም እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሽሽ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን ተባባሉ።

5፤ ጨለምለም ባለ ጊዜ ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ማንም አልነበረም።

6፤ እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሰረገላና የፈረስ የብዙም ጭፍራ ድምፅ አሰምቶ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም። እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ የኬጢያውያንና የግብጻውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል ይባባሉ ነበር።

7፤ ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ።

8፤ እነዚህም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ ጠጡም፥ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፥ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፥ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ።

9፤ ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው። መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምስራች ቀን ነው፥ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተ ሰብ እንናገር ተባባሉ።

10፤ መጥተውም። ወደ ሶርያውያን ሰፈር መጣን፥ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ሰው አልነበረም፥ የሰውም ድምፅ አልነበረም ብለው ወደ ከተማይቱ ደጅ ጠባቂ ጮኹ።

11፤ የደጁም ጠባቂዎች ጠሩ፥ ለንጉሡም ቤት ውስጥ አወሩ።

12፤ ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ባሪያዎቹን። ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ። ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፥ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል አላቸው።

13፤ ከባሪያዎቹም አንዱ መልሶ። በከተማ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እንደ ቀሩት እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፥ እንዳለቁ እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እንስደድም፥ እንይም አለ።

14፤ ሁለትም ሰረገሎች ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም። ሄዳችሁ እዩ ብሎ ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ ላከ።

15፤ በኋላቸው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ ነበር። መልእክተኞችም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት።

16፤ ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸመተ።

17፤ ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን አለቃ በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ ንጉሡም ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው ሞተ።

18፤ የእግዚአብሔርም ሰው ለንጉሡ። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድም መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸመታል ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ።

19፤ ያም አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? ብሎ ነበር፤ እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም ብሎት ነበር።

20፤ እንዲሁም ደረሰበት፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።